ለጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ሰራተኞች በኤች.አይ.ቪ/...

image description
image description
- Recent News   

ለጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ሰራተኞች በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ

የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ሰራተኞች በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ወቅታዊ የስርጭት ሁኔታ፣ የመከላከል እና የመቆጣጠር ስልቶች ዙሪያ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ።

የዕለቱን የስልጠና መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የማዕከሉ የምርምር ልማት ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ደበላ ብሩ በመክፈቻው ኤችኤ ቪ ኤድስ በአለም አቀፍ እና በሀገራችን በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋቱን እና ከሚሰጠው ስልጠና ከበሽታው ራስን እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል እና ልናደርጋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎችን አስመልክቶ የተዘጋጀውን ስልጠና እንዲሰጡ ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የጤና ባለሙያ የሆኑት አቶ ስንታየሁ ጎሹን ወደ መድረክ ጋብዘዋል፡፡

በስልጠናው በዓለም አቀፍና በኢትዮጵያ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ወቅታዊ ሁኔታ፣ ለስርጭቱ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ የባህሪ፣ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ምክንያቶች፣ እንዲሁም በተለይ በከተማ አካባቢዎች የሚታዩ ተጋላጭነቶች በስፋት ተዳሰዋል።

በመድረኩ የቀረቡ መረጃዎች መሰረት ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ አሁንም በዓለም አቀፍና በሀገራችን የህዝብ ጤና ፈተና ሆኖ መቀጠሉ ተገልጿል። በተለይም በአዲስ አበባ የስርጭት ምጣኔ ከሌሎች ክልሎች አንፃር ከፍተኛ መሆኑ ተጠቁሞ፣ ይህንን ሁኔታ ለመቀየር የሁሉም ወገኖች የተቀናጀ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል።

በስልጠናው ወቅት የአባላዘር በሽታዎች ከኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ጋር ያላቸው ቁርኝት፣ የበሽታዎቹ ምልክቶችና የመከላከያ መንገዶች በዝርዝር የተብራሩ ሲሆን፣ ቀድሞ ምርመራ ማድረግ፣ ኮንዶምን በአግባቡ መጠቀም፣ የጤና ትምህርትን ማጠናከር እና ህክምናን በወቅቱ ማግኘት ለመከላከል ወሳኝ መሆናቸው ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪ ከኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ጋር ተያይዞ የሚታየው መገለልና መድልዎ በቫይረሱ ተጠቂ ዜጎች ላይ የሚያስከትለው ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ጫና ተወያይቶበታል። ተሳታፊዎችም የቫይረሱ ተጠቂዎችን መብት ማክበር፣ ማግለልና መድልዎን መዋጋት እና ግልፅ ውይይት በማድረግ ግንዛቤን ማስፋት እንደሚገባ ተገንዝበዋል።

በመጨረሻም የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ሰራተኞች በስራ ቦታና በማህበረሰብ ውስጥ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባራትን በንቃት ለመደገፍ እንዲሁም የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎችን ለማጠናከር ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል።