"ተስፋን እንተከል!" በሚል መሪ ቃል 8ኛው ሀገር አቀፍ አረንጓዴ አሻራ መርሀግብር በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል ተካሄደ
"ተስፋን እንተከል" በሚል መሪ ቃል 8ኛው ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል በደማቅ እና በከፍተኛ ተሳትፎ ተካሂዷል።
በዕለቱም የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጉተማ ሞረዳ የተገኙ ሲሆን የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የአገራችንን አረንጓዴ ሽፋን ለማስፋት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ የተፈጥሮ ሀብትን ለመጠበቅ እና ለቀጣዩ ትውልድ ጤናማና ዘላቂ አካባቢ ለማውረስ የሚደረግ ሀገራዊ እንቅስቃሴ መሆኑ በመግለጽ መርሀ ግብሩን በይፋ አስጀምረዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የማዕከሉ የምርምር ልማት ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ደበላ ብሩ የዛሬ የችግኝ ተከላ ተግባር የነገውን አረንጓዴ ኢትዮጵያ የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸው፣ በተከሉት ችግኞች ላይ ቀጣይ እንክብካቤ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የችግኝ ተከላ ብቻ ሳይሆን የተከሉትን ችግኞች በአግባቡ በመንከባከብ ውጤታማ ማድረግ እንደሚጠይቅም ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም የሆርቲካልቸር ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መክብብ ማሞ ላለፉት ተከታታይ ዓመታት እየጨመረ የመጣውን የችግኝ አተካከል ሂደት በተመለከተ ማብራሪያ ካደረጉ በኋላ በበጀት ዓመቱ 51500 ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን በዛሬው ዕለትም 1500 ችግኞች እንደሚተከሉ እና ከእነዚህም ውስጥ ከስድስት አይነት በላይ የሚሆኑት የፍራፍሬ ችግኞች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ለአፈር እና ውሀ ጥበቃ ስራዎች የሚያግዙ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ ችግኝ ተከላውን በተመለከተ ለሚደረገው ጥንቃቄ የስራ ክፍሉ ሆርቲካልቸራሊስት ባለሙያ አቶ ትርፉ ኦላና ሙያዊ የችግኝ አተካከል ሂደትን ለሰራተኛው በማሳየት ችግኞቹን የመትከል ስራው የተከናወነ ሲሆን በማዕከሉ የለማ የከተማ ግርብርና ቱሩፋት የተገኘ ምርት ለሰራተኛው በማከፋፈል የዕለቱ ፕሮግራም ተጠናቋል፡፡