የጳጉሜን 5 የነገ ቀንን አስመልክቶ በጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል “የላቀ አገልግሎት አሰጣጥ ለህዝባዊ አመኔታ!” በሚል ርዕስ ሰነድ ቀረበ፡፡
የውይይት መድረኩን የማዕከሉ የኢኮቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ሞገስ አባተ የመክፈቻ ንግግር በማድረግ ያስጀመሩ ሲሆን፣ የተቋሙ የምርምር ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ደበላ ብሩ የተዘጋጀውን ሰነድ በስፋት አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ የማዕከሉ የሥራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች በተሳተፉበት በአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በተጠቃሚዎች እርካታ እና በህዝብ አመኔታ ግንባታ ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።
በቀረበው ሰነድ መሰረት የነገዋን ኢትዮጵያ በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት የዛሬው አገልግሎት አሰጣጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተጠቁሟል። በተለይም የተገልጋዮችን ፍላጎት መረዳት፣ ግልጽና ፈጣን አገልግሎት መስጠት፣ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እና ዘመኑን የዋጀ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ የህዝብ አመኔታን ለመገንባት ቁልፍ ጉዳዮች መሆናቸው ተነስቷል።
የነገ ቀን መከበሩም የተሻለ ነገን ለመገንባት ዛሬ ላይ ተግባራዊ ለውጦችን ማምጣት እንደሚገባ ለማስገንዘብ ያለመ መሆኑ ተጠቁሟል። በዚህም በጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል የሚሰጡ አገልግሎቶችን በቀጣይነት በማሻሻል፣ የተገልጋዮችን እርካታ በማሳደግ እና ለተሻለ አፈጻጸም በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት ተገልጿል፡፡ በመጨረሻም በሰነዱ ላይ ከሰራተኛው ሀሳብ እና አስተያየት በመቀበል ውይይት በማድረግ የእለቱ ፕሮግራም ተጠናቋል፡፡