የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት ሃይማኖታዊና ባ...

image description
- Recent News   

የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው በሰላም እንዲከበሩ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅትና የጋራ መግባባት ሥራዎች ዙሪያ ውይይት ተካሄደ

መድረኩን የከፈቱት የዕለቱ የክብር እንግዳና የጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል የምርምር ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ደበላ ብሩ ሲሆኑ በንግግራቸውም የበዓላቱ ሰላማዊ አከባበር ለሕዝቦች አብሮነት፣ መቻቻልና የጋራ እሴቶች መጠናከር ያለውን አስተዋፅኦ በመገንዘብ በቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ላይ በትኩረትና በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የበዓላቱን አከባበር አስመልክቶ የተዘጋጀውን ሰነድ በዝርዝር ያቀረቡት የማዕከሉ አማካሪ አቶ ፋሩቅ ጀማል ሲሆኑ በማብራሪያቸው፣ መስቀል ደመራና ኢሬቻ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአብሮነት፣ የወንድማማችነት፣ የእርስ በርስ መከባበርና የባህል ብዝሃነት መገለጫዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል። በዓላቱ ለሰላም፣ ለአብሮነትና ለማሕበራዊ ትስስር መጠናከር ያላቸውን ሚና በማጉላትም ለበዓላቱ ሰላማዊና የተሳካ አከባበር የሚያስፈልጉ የቅድመ ዝግጅት፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የትብብርና የተሳትፎ ሥራዎች በተቀናጀ መልኩ መከናወን እንዳለባቸው ገልጸዋል።

እንደ አቶ ፋሩቅ ገለጻ በዓላቱ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን በስፋት የሚስቡ በመሆናቸው ሰላማዊና የተሳካ አከባበራቸው ለሀገሪቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴና ለኢትዮጵያ ባህላዊ እሴቶች ተገቢውን ገጽታ ለማስጠበቅ ጠቃሚ መሆኑንም ጭምር አስገንዘበዋል፡፡

በውይይቱ ተሳታፊዎችም የበዓላቱ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶች እንዲጠበቁ የሰላምና የአብሮነት መንፈስ እንዲጠናከር በዓላቱን ለማክበር የሚመጡ ጎብኚዎችም ምቹና ሰላማዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ሊከናወኑ በሚገቡ ተግባራት ዙሪያ ሃሳቦችን አንስተዋል።

በመጨረሻም የማዕከሉ ሰራተኞች መጪዎቹ የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት ሰላማዊ፣ ደማቅና ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ የተጀመሩ የቅድመ ዝግጅትና የጋራ መግባባት ሥራዎችን በትብብር ማጠናከር እንደሚገባ ሀሳብና አስተያየት በመስጠት የዕለቱ ፕሮግራም ተጠናቋል፡፡