የጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል የ2019 ዓ.ም የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ተወያየ
የጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል በ2019 ዓ.ም የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራትና የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ለማዕከሉ አመራሮችና ሠራተኞች አቅርቦ ሰፊ ውይይት አካሂዷል።
በማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጉተማ ሞሮዳ በተከፈተው በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የሩብ ዓመቱን የተግባር አፈፃፀም ዝርዝር ሪፖርት የዕቅድና በጀት ክትትል ግምገማ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ምስክር ታዬ አቅርበዋል። የቀረበው ሪፖርት የማዕከሉን የአራቱን ዓላማ ፈፃሚ እና የደጋፊ ዳይሬክቶሬቶችን እንቅስቃሴ በጥልቀት ዳስሷል።
በመድረኩ በተካሄደው ውይይት የሩብ ዓመቱ አጠቃላይ የሥራ አፈፃፀም አበረታች መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በሥራ ሂደት የታዩ ጥንካሬዎችን አጠናክሮ ማስቀጠልና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመገምገም ለቀጣይ ሥራዎች እንደ ጠቃሚ ግብዓት መጠቀም እንደሚገባ ተመልክቷል። በማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጉተማ ሞሮዳ እና በምርምር ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ደበላ ብሩ መሪነት በተካሄደው በዚህ መድረክ ከተለያዩ የሥራ ክፍሎች ዳይሬክተሮችና ባለሙያዎች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶችም ተገቢው ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቷል። በመጨረሻም የታዩ ክፍተቶችን በማረም በቀጣይ ዕቅዶችን በተሻለ ቅንጅት ለመፈፀም በመስማማት የዕለቱ ወይይት ተጠናቋል።