የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ
በጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል ለማዕከሉ ሰራተኞችና አመራሮች በመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ።
ስልጠናው በመንግስት ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ ተጠያቂና ውጤታማ ለማድረግ የሚደረጉ የሪፎርም ሥራዎች፣ የሰው ሀብት አስተዳደር፣ የብቃትና ምዘና ሥርዓት እንዲሁም የሰራተኞችን ውጤታማነት በማሳደግ ረገድ በሪፎርሙ የሚጠበቀውን ሚና ያተኮረ ነበር።
ስልጠናውን ያስጀመሩት የጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል የምርምርና ልማት ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ደበላ ብሩ ሲሆኑ፣ ስልጠናውን የሰጡት የፐብሊክ ሰርቪስ የሰው ሀብት አስተዳደር የብቃትና ምዘና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌቱ ቱፋ ናቸው።
በስልጠናው ወቅት ሰልጣኞች ከሪፎርሙ ይዘትና ከተግባራዊ አፈጻጸሙ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ጥያቄዎችንና ሀሳቦችን አንስተዋል። በተነሱት ጥያቄዎች ላይም አሰልጣኙ አቶ ጌቱ ቱፋ በሙያዊ እውቀታቸውና በተግባራዊ ልምዳቸው ላይ በመመስረት ዝርዝርና ግልጽ ማብራሪያዎችን በመስጠት የተሳታፊዎችን ጥያቄዎች መልሰዋል።
ይህም ስልጠናውን የበለጠ ተሳትፎ ያለበትና ተግባራዊ በማድረግ፣ ተሳታፊዎች የሪፎርሙን አላማ፣ አተገባበርና ከዕለት ተዕለት የስራ አሰራራቸው ጋር ያለውን ትስስር በተሻለ ሁኔታ እንዲረዱ አስችሏል።
በመጨረሻም በስልጠናው የተገኘው ግንዛቤ በማዕከሉ የስራ አፈጻጸምን፣ ተጠያቂነትንና ተገልጋይ ተኮር አገልግሎትን በማሳደግ የሪፎርሙን ዓላማ በተግባር ለማሳካት ጠቃሚ መሆኑ ተገልጿል።