“ለሀገር ድምቀት የቀለማት ህብረት” በሚል መሪ ቃል የስዕል አውደርዕይ ተከፈተ
በአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል ጋር በመተባበር “ለሀገር ድምቀት የቀለማት ህብረት” በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው የስዕል አውደርዕይ ዛሬ በይፋ ተከፍቶ ለዕይታ በቅቷል፡፡ በርካታ ወጣትና አማተር ሰዐልያን የተሳተፉበት ይህን አውደርዕይ መረቀው የከፈቱት የጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጉተማ ሞሮዳ ሲሆኑ የዕፅዋት ማዕከሉ ካሉት አምስት አላማዎች አንዱ አካባቢን መሰረት ያደረገ የኢኮቱሪዝም አገልግሎት መሆኑን ጠቅሰው የስዕል አውደርዕይ ለማዘጋጀት ምቹና በርካታ አስቻይ ሁኔታዎች አሉት ብለዋል፡፡ከከተማው ባህል፣ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በርካታ ስራዎችን ማዕከሉ ያከነወነ ሲሆን በቀጣይ የተሻለ ሥራዎችን ለመስራት የሚያስችል የቅንጅት ስምምነት ሲላለ ተጠናክሮ የቀጥላል ብለዋል፡፡የባህል፣ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የኪነጥበብ ሀብቶች፣መድረኮች፣ሁነቶች ዝግጅት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሰለሞን ደጉ በበኩላቸው የስዕል አውደርዕዩ ሲዘጋጅ ለስድስተኛ ጊዜ መሆኑን ጠቅሰው የዕፅዋት ማዕከሉ ሁነቱ ባማረ ስፍራ እንዲካሄድ በመተባበሩ አመስግነዋል፡፡አውደርዕዩ በይፋ ተመርቆ ሲከፈት የማዕከሉና የቢሮው የሥራ ኃላፊዎች፣ሠራተኞች፣ጥሪየተደረገላቸው እንግዶችን ተማሪዎች ተገኝተው ጎብኝተዋል፡፡አውደርዕዩ ለስድስት ተከታታይ ቀናት ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚሆን ታውቋል፡፡