የ2018 ዓ.ም የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላት አ...

image description
- Recent News   

የ2018 ዓ.ም የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላት አከባበር በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ውይይት ተደረገ

የጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል አጠቃላይ ሰራተኞች በያዝነው ወር አጋማሽና በወሩ መጨረሻ በሚከበሩ የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት አከባበር ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበረ በቀረበ ሰነድ ላይ ውይይት አደረጉ፡፡

የውይይት መድረኩን የማዕከሉ የኢኮቱሪዝም ልማት ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሞገስ አባተ የከፈቱ ሲሆን በአለም አቀፍ የቅርስ መዝገብ ላይ የተመዘገቡትን የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላትን እሴቶቻቸውን እና ትውፊታቸውን ጠብቀው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገሩ በጋራና ሰላማዊ በሆነ መንገድ በማክበር ኢትዮጲያ ሀገር በቀል እምነቶች እና ጥንታዊ ሀይማኖቶች ተቻችለው የሚኖሩባት ምድር መሆኗን በአለም አደባባይ የሚያስመሰክር በመሆኑ በዓላቱን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ማክበር ለከተማችንና ለሀገራችን የኢኮኖሚና ቱሪዝም ዕድገት ምንጭ ለማድረግ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል፡፡

የዘንድሮውን መስቀልና ኢሬቻ በዓላትን ከአባቶቻችን በጀግንነት የወረስናትን ሉአሏዊ የሆነችውን ሀገራችንን ከውጪ እና ከውስጥ ጠላቶች በመከላከል ሀገራዊ አንድነታችንን ለማጽናት ቃል የምንገባበት እና ዳግማዊ ዓድዋ የሆነውን የህዳሴ ግድባችንን በተረባረበ ክንዳችን ማጠናቀቃችን ባበሰርንበት ማግስት መሆኑ በዓላቱን ልዩ እንደሚያደርጋቸው በሰነዱ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የከተማ ትራንስፎርሜሽን አካል የሆነው የኮሪደር ልማት የወንዞች ዳርቻ ልማት መጠናቀቅ በዓላቱን ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጪ ጎብኚዎች ምቹ የቱሪስት መዳረሻ እንደሚያደርጋት ተገልጿል፡፡

በመጨረሻም በዓላቱ የሚከበሩበትን ቦታዎች በጽዳት ዘመቻ ላይ በመሳተፍ፤ ለሰላም ልዩ ትኩረት በመስጠት እና እንግዳ ተቀባይነት ባህላችንን ይበልጥ በማጠናከር ማክበር ይገባል በማለት ሰነዱን የማዕከሉ የምርምር ልማት ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ደበላ ብሩ በሰፊው አቅርበዋል፡፡