“ሥነጥበብ እና ተፈጥሮ “ በሚል መሪ ቃል የሚካሄው ሁነት ተጀመረ
ጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ኪነጥበብ ቢሮ ጋራ በመተባበር “ሥነጥበብ እና ተፈጥሮ “ በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀውን ሁነት የማዕከሉ የኢኮቱሪዝም ልማት ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሞገስ አባተ እና የምርምር ልማት ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ደበላ ብሩ በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተከፈተ፡፡
በሁነቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የማዕከሉ የኢኮቱሪዝም ልማት ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሞገስ አባተ ይህ ሁነት በማዕከሉ ውስጥ መደረጉ ተፈጥሮ ከስነ ጥበብ ጋር ያለውን ቁርኝት በመግለጽ ማዕከሉን ለማስተዋወቅ የራሱ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡
በመቀጠል የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብ ቢሮ የኪነጥበብ ዘርፍ ምክትል ሃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ሉባባ ጀማል ይህ የስዕል ዐውደ ርዕይ የሀገራችንን ባህል እና ኪነጥበብ ለማስተዋወቅ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን በመግለጽ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል ውስጥ ያሉ ሰዓሊያንን ለማበረታታት እድሉን እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
በሁነቱም የስዕልና የፎቶግራፍ አውደርዕይ እንዲሁም የተለያዩ የእደጥበብ እና እጅ ስራዎች የሚጎበኙ ሲሆን በቀጣይ ቀናትም በርካታ ጎቢኚዎች እንደሚሳተፉበት ተገልጿል፡፡ ሁነቱ ከሕዳር 4 - ሕዳር 14 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚሆን ታውቋል፡፡