ማዕከሉ ከጉለሌ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎች ጋር በቅንጅት ለመስራት ውይይት አደረገ
የዕለቱን መድረክ የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጉተማ ሞሮዳ የከፈቱ ሲሆን በጉለሌ የዕፅዋት ማዕከል የቱሪዝም ልማት እና ፕሮሞሽን ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ ስለማዕከሉ አጠቃላይ የቦታው ስፋት፤ የቦታ አቀማመጥ፤ የአጥር ሁኔታ እና የዕፅዋት ሽፋንን በተመለከተ አጭር ሰነድ ቀርቧል፡፡
በዕለቱም በማዕከሉ ውስጥ የሚስተዋሉትን ችግሮች ለመፍታት ከኛ ምን ይጠበቃል እናንተስ ምን ያህል ከማዕከሉ ጋር አብራችሁ እየሰራችሁ ነው በማለት ውይይቱን ዋና ዳይሬክተሩ ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከኮማንደር አብይ መብራቱ ጋር በጋራ አስጀምረዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ፤ ከአስኮ ፖሊስ ጣቢያ፤ ከፓስተር ፖሊስ ጣቢያ እና ከወረዳ 8 ፖሊስ ጣቢያ፤ በመጡ የፖሊስ ኃላፊዎች የተለያዩ ሃሳቦች የተነሱ ሲሆን ከተነሱት ውስጥ የፖሊስ አባላቱ ከማዕከሉ የጥበቃ አባላት ጋር መልካም የስራ ግንኙነት እንዳላቸው በመግለጽ ማዕከሉ ውስጥ ወንጀል ይፈጸምባቸዋል የተባሉትን የስጋት ቀጠናዎች በመለየት የፖሊስ ኃይሎችን ፤ ሲቪል ክትትሎችን በመመደብ ፤ በሳምንት ሁለት ቀናት አሰሳ በማድረግ እና በማዕከሉ ውስጥ በሚደረጉ ፕሮግራሞች ላይ የፖሊስ ኃይሎችን በመመደብ ጭምር እየሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በመቀጠል ማዕከሉ እጅግ ሰፊ እና ለጥበቃ ምቹ ያልሆኑ ቦታዎች በውስጡም እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን በማዕከሉ በኩል ቢስተካከል ያሉትን ሃሳቦች ተነስተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በተለያዩ ቦታዎች ላይ የተዘጋጁ የእንግዳ ማረፊያ መቀመጫዎች ለማንሳት ምቹ በመሆናቸው ወደመሬት ተቀብረው የሚቀመጡበት ሁኔታ ቢፈጠር ፤ በማዕከሉ ውስጥ የሚገኙ ንብረቶች ለምሳሌ ቁርጥራጭ የኤሌክትሪክ ገመዶች የመሳሰሉት ተሰብስበው ቢነሱ በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በተጨማሪ የማዕከሉ የኢኮ ቱሪዝም ልማት ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሞገስ አባተ በሰጡት አስተያየት ከላይ የተገለጹትን በማዕከሉ በኩል ያሉትን ክፍተቶች ለማስተካከል ዝግጁ መሆናቸውን እና በቀጣይ ሊታሰብበት ይገባል ያሉትን የስርቆት ወንጀል እንዴት ከፖሊስ አባላት ጋር ተቀናጅተን መሰራት እንዳለበት አስተያታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የማዕከሉ አማካሪ አቶ ፋሩቅ ጀማል የአካባቢው የፖሊስ አባላት ማዕከሉን በዚህ ልክ ማወቃቸው አብረው በጋራ እንደሚሰሩ ማሳያ መሆኑን በመግለጽ የተነሱትንም ሃሳቦች በቀጣይ በዕቅዳችን ውስጥ በማካተት በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም ዋና ዳይሬክተሩ ለተደረገው ትብብር ምስጋናቸውን በማቅረብ ከላይ የተነሱትን አስተያየቶች ወስደን በቀጣይ በማዕከሉ ውስጥ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ በዋናነት የፖሊስ እገዛ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ የዕለቱን መድረክ አጠናቀዋል፡፡